የቅማንት ሕዝብ አቤቱታ
የቅማንት ብሔረሰብ ተወላጆች
ይድረስ ለተከበሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሣ ተክለ ብርሃን
ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች፣ ሃይማኖቶች፣ ወጎችና ልምዶች ያሏቸው የተለያዩ ሕዝቦች ለረዥም ጊዜ የኖሩባትና እየኖሩባት ያለች አገር ናት። በዚህ አብሮ የመኖር ሒደት እነዚህ ሕዝቦች የተለያዩ ክፉና በጎ ነገሮችን አስተናግደዋል፡፡ በጋራም የጋራ የሚሏቸውን በግል ደግሞ የግል የሚሏቸውን መገለጫዎች ይዘው ‹‹ኢትዮጵያዊ›› በሚለው መጠሪያቸው ለዘመናት አብረው ኖረዋል።
ግን በኢትዮጵያ የነበረው ታሪክና እውነታ የሚያሳየን ሕዝቦች የአገራቸው ባለቤት ሳይሆኑ፣ በዘራቸው ተንቀውና እትብታቸው በተቀበረበት ቀየ ገባር ሆነው ማሳለፋቸው ማንም የማይክደው ሀቅ ነው፡፡
እነዚህ እንደ ሕዝብ በዘር ስማቸው እንዲታወቁ የማይፈለጉ ሕዝቦች ገዥዎች በተዋረድ በሚሾሟቸው ባለሟልና አሽከሮቻቸው አማካይነት ሕዝቦች ከዘር ስማቸው ጀምሮ ቋንቋቸውን፣ ሃይማኖታቸውን፣ ባህላቸውንና የመጨረሻ የሆነውን በራሳቸው ቋንቋ የወጣላቸውን የግል መጠሪያ ስማቸውን እንኳ ሳያስቀሩ እንዲቀይሩ ተገደዋል፡፡ በዚህ ሕዝብን የማቅናትና ወደ አንድ ዓይነት የሕዝብ ስም፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ባህል የማምጣት ሒደት የሌላ ማንነት በግዳጅ በላያቸው ላይ ተጭኗል:: ቋንቋቸውን እንዳይናገሩ ስለተደረገ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋና እንዲዳከም ተደርጓል፡፡
ይህን የማንነትና የዕምነት የኃይል ገፈፋ በጦርነት ለመከላከል የሞከሩ አንዳንድ ሕዝቦች በመጨረሻ ተሸንፈው በአገራቸው ላይ ተዋርደውና ተንቀው፣ የዕለት ጉርስ ሊያመርቱ የሚችሉበት ስንዝር መሬት ተነፍገው እንዲፈልሱና እንዲበታተኑ ተደርገው፣ ያለስማቸው የስድብ መጠሪያ ስም ተሰጥቷቸው በድህነት መኖር ዕጣ ፈንታቸው ሆኖ ኖሯል።
ከላይ በመጠኑ ለመግለጽ የተሞከረውን ግፍና በደል ከተጋቱትና ከአስተናገዱት የኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የቅማንት ብሔረሰብ አንዱ ነው፡፡ የቅማንት ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን በተለየ የዚያ የግፍ ሥርዓት የመጀመሪያውና ዋና ተጋላጭ የነበረና ከባድ የሆነ የሃይማኖት፣ የአገዛዝ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የሥነ ልቦና ተጽዕኖ ለረዥም ዘመናት አርፎበታል፡፡ ይህ የግፍ ሥርዓት አስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን የፊውዳል ሥርዓት ድረስ በመዝለቅ በቅማንት ሕዝብ አጠቃላይ ማንነት ላይ የማይጠፋ መጥፎ አሻራውን አሳርፎ አልፏል፡፡
የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶችና መታፈን ከብሔሮችና ብሔረሰቦች መብት መታፈን ጋር የተያያዘ ጉዳይ በመሆኑና ግፉ ሕዝቦች ሊሸከሙት ከማይችሉት ደረጃ በመድረሱ፣ ያን ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ በማስወገድ በምትኩ ሁሉም ብሔረሰቦች፣ ብሔሮችና ሕዝቦች በእኩልነት ማንነታቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ጠብቀው በአንድነት የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችላቸው ሥርዓት መገንባት አማራጭ የሌለው በመሆኑ፣ ይህን እውን ሊያደርግ ወደሚያስችለው ሥርዓት አምርተዋል፡፡ የዚያ የረዥም ጊዜ የሕዝቦች ተጋድሎ ውጤትም አሁን በመተግበር ላይ ያለው የፌዴራል ሥርዓት ነው፡፡
የፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መነሻ ሐሳብ በሕዝቦች መካከል በመፈቃቀድና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ዲሞክራሲያዊ አንድነትን መፍጠርና ይህ አንድነታችን ግን የየብሔረሰቦች እሴቶችን በአስተዳደራዊ መንገድ በመደምሰስ በአንድ ሕዝብ ስም እንዲጠፉና እንዲዋጡ ለማድረግ፣ አንድነቱ ሕዝቦችን አንድ ላይ በማድረግ ሰፊ የግዛት አስተዳደራዊ ትስስር ለመፍጠር ሳይሆን በጋራ ዓላማ፣ በጋራ እሴቶች ላይ የተመሰረተ አንድነት ማምጣት ነው፡፡
ይህን ሀቅ መሰረት በማድረግ ሕገ መንግሥቱ በመግቢያው ላይ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› በማለት የሕገ መንግሥቱ ዋነኛ ምሰሶዎች የተለያዩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ እንዳስቀመጠው አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚቻለው የግለሰቦችና የብሔር ብሔረሰብ መሠረታዊ መብቶች በእኩልነት ሲከበሩ ብቻ ነው ይላል፡፡
ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው በአንቀጽ 39 በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አንቀጽ 39 ሕዝቦች እኩልነታቸው እንዲጠበቅ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ በጋራ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ በእኩልነትና ሚዛናዊ በሆነ አኳኋን እንዲወከሉ፣ ብሔረሰባዊ እሴቶቻቸውን እንዲያዳብሩ ይፈቅዳል፡፡ በዚህም መሠረት ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፋቸውን መብት በመጠቀም ተረስተው የነበሩ አያሌ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላለፉት 20 ዓመታት በማንነታቸው ኮርተው አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ በመጀመራቸው ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደርና ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ቋንቋቸውን በመንከባከብና በማሳደግ ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸው በግልጽ በሕገ መንግሥቱ ይቀመጥ እንጂ፣ ዛሬም ድረስ ‹‹እኔ አውቅልሀለሁ›› በሚሉ ጮሌዎች የሁሉም ብሔረሰቦች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል ከሚያስብል ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ በተለያዩ የፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በ20 ዓመታት የፌዴራል ሥርዓት ጉዞ መብታቸው ሳይረጋገጥ እንዲያውም ካለፈው ሥርዓት በባሰ መልኩ በደባል ማንነትና በሰቆቃ ውስጥ እንዲማቅቁ ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ማንነታቸው በሌላ ማንነት ሥር እንዲወድቁ የተደረጉ ሕዝቦች ወገን መሆናቸው ፍፁም ተዘንግቶ የተዛባና የጠባብ አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ሰለባ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡
ያለፈው የግፍና የአፈና ሥርዓት ጠባሳ ሳይሽርላቸው በዚህ የፌዴራል ሥርዓት ከሌላው ሕዝብ ተለይተው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተነፍጎ በሌላ ማንነት ሥር እንዲወድቁና ለዳግም የማንነት ቀውስ ከተዳረጉ ሕዝቦች መካከል፣ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚገኘው የቅማንት ብሔረሰብ አንዱ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ለዚያ ሕዝባዊ የነፃነት ትግል ከአብራኩ የወጡ ልጆቹን ወዶና ፈቅዶ መስዋዕት እንዳላደረገ ሁሉ፣ ያለፈው ጨቋኝ ሥርዓት ዋነኛ ተጠቂ እንዳልነበረ ሁሉ፣ ይህ ሕዝብ ራሱን የቻለ ሕዝብ እንዳልሆነ ተቆጥሮ ዛሬም ድረስ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ተነፍጎ በደባል ማንነት እንዲቀጥል ተፈርዶበታል፡፡ ማንነት በአንድ ሕዝብ ላይ በሌላ አካል ከውጭ የሚጫን ግዴታ ሳይሆን በሕዝቦች ሙሉ ፍላጎት ብቻ የሚወሰን ለመሆኑ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ታዲያ የቅማንት ሕዝብ ያልሆነውን ነህ የተባለበት መነሻ ምክንያቱ ምን ይሆን?
ክቡር አፈ ጉባዔ
እርስዎ በሚመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ከሚገኙት የ75 ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች መካከል የቅማንትን ብሔረሰብ ወክሎ የተቀመጠ አንድም ተወካይ እንደሌለ ያውቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ በቅማንት ሕዝብ ቁጥር ምክንያት ተጨማሪ የፌዴሬሽን ውክልና የተጎናፀፉ ቅማንት ያልሆኑ ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ምክንያት እርስዎ የሚመሩት ምክር ቤት እንደቅማንት ያለ ብሔረሰቦችን አግልሎ የተቋቋመ በመሆኑ ብቻ በተሟላ መልክ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ነው ሊያስብለው አይችልም፡፡
እርስዎ የተገኙበትና በከፍተኛ ደረጃ ውሳኔ ሰጭነት አሁንም ድረስ አባል ሆነው የሚመሩት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የቅማንት ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን እንዳይጎናጸፍ ውኃ የማይቋጥሩና ተራ ምክንያቶችን በመደርደር በንቃት እየሄደበት ለመሆኑ እርስዎም የሚያውቁት ጉዳይ ነው፡፡
የቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ምላሽ መዘግየት በግልጽ የሚያሳየው በብአዴን የድርጅት መዋቅር ሥር የተኮለኮሉ የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ለፌዴራል ሥርዓቱ ምን ያህል አደጋ መሆናቸውን ነው፡፡ ዛሬ ሕገ መንግሥቱንና የፌዴራል ሥርዓቱን ለመናድ ያላቸውን ስውር ዓላማ እያፈራረቁ ለመጠቀም የሚሞክሩ አንዳንድ የብአዴን ካድሬዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ ከአሮጌው ሥርዓት የዞረ ድምር (hangover) ሙሉ በሙሉ ያልፀዱና ያን የግፍ ሥርዓት ለመመለስ መቃብር የሚቆፍሩ አንዳንድ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች፣ የቅማንትን ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ‹‹የአገው ዳይናስቲን›› ለመመለስ እንደሚታገል አድርገው በመቁጠር፣ በተለያዩ መድረኮች በግልጽ በመናገር የሌላውን ሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሲጥሩና አለፍ ሲልም በግልጽ በማስፈራራትና በማሰር፣ የፌዴራል ሥርዓቱን ምሰሶ ለማናጋት የአገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ለመጠቀም ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በጎጥና በአካባቢ ተጠራርተው በመደራጀት ላይ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ጥቂት የብአዴን አመራሮች በኢትዮጵያ ሕዝቦች ተጋድሎ የተረጋገጠውን ሕገ መንግሥት እንዲያስፈጽሙ በሕዝብ የተሰጣቸውን አደራ ዘንግተው የቅማንትን ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄ እንዳይሳካ የሚዶልቱ ቡድኖችንና ግለሰቦችን (በውጭ አገርና በአገር ውስጥ) በስውር በማደራጀትና በመምራት፣ በመንግሥት ላይ አላስፈላጊ ጫና ለመፍጠርና የዚህ ሕዝብ ጥያቄ መስመሩን እንዲስት ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በየዓለም አቀፍ ስብሰባና መድረክ በኢትዮጵያ መሪዎች ላይ በተለያየ ጊዜ የሚካሄደው ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሠልፍ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ቀጥተኛ አጀንዳ ነፀብራቅ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ ድርጊት በውሸት አንድነት ስም በሕገ መንግሥቱ አማካይነት ሀራ የወጡ የኢትዮጵያን ሕዝቦችን ወደ ድሮው የብሔረሰቦች እስር ቤት የመመለስ ድብቅ ሴራ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ስም ሊሰጠው አይችልም፡፡
የተከበሩ አቶ ካሳ
የቅማንት ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 (5) ሥር የተቀመጠውን አንድን ሕዝብ የተለየ ብሔር ሊያስብሉ የሚችሉ መስፈርቶችን በትክክል የሚያሟላ መሆኑ እየታወቀ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ ማደናገሪዎችን በመጠቀም ዛሬም ድረስ የዚህ ሕዝብ መብት እንዳይከበር በማድረግ እርስዎ በአፈ ጉባዔነት የሚመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተልዕኮ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ለማድረግ የበኩላቸውን አሉታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
የቅማንት ሕዝብ ወጥ በሆነና በተያያዘ መልክዓ ምድር እንደሚኖር በግልጽ እያወቁ ከአማራው ሕዝብ ጋር ተቀላቅሎ የሚገኝ በመሆኑ ለመለያየት መሞከር አላስፈላጊ ግጭት ያስከትላል የሚል አሉባልታ በመንዛት፣ የሕዝቡን ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብት በመንፈግ በተዛባ የግዛት አንድነት ሥር እንዲወድቅ አድርገውታል፡፡ ግጭት የሚባለው ቅማንት ራሱን በማስተዳደሩ ምክንያት የሚከሰት ወይስ ደግሞ የዚህ ሕዝብ ከሞግዚት አስተዳደር መላቀቅ የሚያበግናቸው ግለሰቦች የሚያስነሱት ግጭት ነው? ይህ ግጭት የሚባለው ሽፋን እነዚህ ለፌዴራል ሥርዓቱ አደጋ የሆኑ አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ካድሬዎች የግል ስሜት ካልሆነ በስተቀር የአማራው ሰፊ ሕዝብ ቅማንት የሚባል ሕዝብ የት እንዳለ ያውቃል፤ ቅማንቱም በተመሳሳይ አማራውን ያውቃል፡፡ ታዲያ ቅማንት ራሱን በራሱ የማስተዳደር የመብት ጥያቄ የግጭት ስጋትነት መነሻው ሕገ መንግሥቱንና የፌዴራል ሥርዓቱን ለመናድ ዳር ዳር ከሚሉና ሥርዓቱን የግጭት ምንጭ በማስመሰል ወደ አሮጌው የጭቆና ሥርዓት ለመመለስ ከሚፈልጉ ትምክህተኛ ግለሰቦች አዕምሮ አስተሳሰብ የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ክቡር አፈ ጉባዔ
ለእነዚህ ጥቂት የብአዴን ባለሥልጣናት የቅማንትን ሕዝብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ለማምታት ከሚጠቀሙበት ሌላው ተራ ምክንያት ቋንቋ ነው፡፡ የዚህ ሕዝብ ቋንቋ እንዴት እንደተዳከመ በግልጽ እያወቁና ማንኛውም ዓይነት ቋንቋ ለለውጥ የተጋለጠ መሆኑን እየተረዱ፣ የዚህን ሕዝብ ማንነት በቋንቋ አሳበው ለማደፈን በተለያየ ጊዜ በግልጽ ሞክረዋል፡፡ ሕዝቦች በቋንቋቸው የመጠቀም መብት አላቸው ማለት የሌላውን ቋንቋ ማወቅና መማር የለባቸውም ማለት እንዳልሆነ ለእነዚህ ግለሰቦች ይጠፋቸዋል የሚል ግምት የለንም፡፡ አንድ ግለሰብ ቋንቋን በውዴታ ወይም ተገዶ ሊማር ይችላል፡፡ አንድ ሰው የሌላ ቋንቋ ተናገረ ማለት ግን ማንነቱ ተቀየረ ማለት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አማርኛ የፌዴራል መንግሥት ቋንቋ እንዲሆን ሲወሰን ይህን ቋንቋ የሚጠቀሙ በሙሉ አማራዎች ናቸው ማለት እንዳልሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት በታሪክ አጋጣሚ አማርኛ ቋንቋ የሚናገሩ ኢትዮጵያዊያን ብዛት ስላላቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚያ አልፎ አማርኛ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን በክልሉ መንግሥት ተመርጧል፡፡ ይህ ማለት የደቡብ ሕዝብ አማራ ነው ማለት አይደለም፡፡ ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መብታቸው የተከበረ ቢሆንም ብሔረሰቦች በነፃ ፍላጎታቸው የሌላ ቋንቋ የመጠቀም ምርጫቸው የተጠበቀ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ቅማንትም ቢሆን ሲፈልግ ከመንትነይን፣ አገዉኛን፣ ትግርኛን፣ አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛን ወይም ሌላ ቋንቋ የመናገርና የማወቅ መብቱ የሚገደብ አይሆንም፡፡
ይህ ሲባል ግን ቅማንትኛ ቋንቋ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ለማለት ሳይሆን፣ አንዳንድ የብአዴን ካድሬዎች የዚህን ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄ ለማደናገር የሄዱትን እርቀት ለማሳየት ብቻ ነው፡፡ የቅማንት ሕዝብ አሁንም ድረስ የሚነገርና ሊያድግ የሚችል ቋንቋ ባለቤት መሆኑን ያውቃሉ፣ ሲነገር ሰምተዋል፣ በአካል ተገኝተውም አረጋግጠዋል፡፡
የተከበሩ አቶ ካሳ
ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ.ም በተከፈተው የመጀመሪያ ዓመት የመክፈቻ ንግግር የቅማንት ሕዝብና የሌሎች ብሔረሰቦች ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ አለመመለሱ እንደ ባለፈው ዓመት አሁንም እንደ ችግር ደግመው ባለማንሳትዎ የምክር ቤቱን ገጽታ ጥላ እንዲያጠላበት ያደርገዋል፡፡ ይህ ሕዝብ በመሪዎቹ አማካይነት ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄውን ለክልሉ መንግሥት በደብዳቤ ከ24 ጊዜ በላይ በአካል ደግሞ ከ10 ጊዜ በላይ ያቀረበ ቢሆንም፣ የክልሉ መንግሥት ግን ጥያቄው ትኩረት የሚሰጠውና ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ መሆኑን በመዘንጋት ከተራ አስተዳደራዊ ቅሬታ በማሳነስ ለጥያቄው የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ በማድበስበስ ላይ ይገኛል፡፡
ምናልባት የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጊዜ አጥተው እንዳይባል የመኪና መንገድ በእኔ በር አላለፈም ብሎ ሰላማዊ ሠልፍ ያደረገ ሕዝብ ዘንድ በአካል በመገኘት ጥያቄውን አስተናግደው ሕዝቡን ይቅርታ ብለዋል፡፡ የቅማንት ሕዝብ ግን ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በማንነቱ ዙሪያ ባደረገው ሕዝባዊ ስብሰባና ኮንፈረስ ላይ በክብር ተጠርተው እንኳ የሕዝቡን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ለመስማት ከክልል እስከ ዞን ድረስ ፍላጎቱ የነበረው አንድም ባለሥልጣን አልነበረም፡፡ ይህ የሚያሳየው አንዳንድ የብአዴን ባለሥልጣናት ለቅማንት ሕዝብ ያላቸውን ግልጽ ንቀትና ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ካላቸው የተደበቀ ዓላማ የሚመነጭ ተግባር ነው፡፡ ምናልባት ከቅማንት ሕዝብ የሚጠበቀው ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ መብቱን እንዲጠይቅ ሳይሆን፣ ከሕዝብና ከመንግሥት ጆሮ የሚደርስ የተለየ እንቅስቃሴ ከሆነ ከዚህ ባለፈ ሊያደርግ እንደሚችል ለካድሬዎቹ ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን፡፡
የዚህ ሕዝብ ጥያቄ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያገኙትን ሕገ መንግሥታዊ መብት መጎናፀፍ መሆኑ በግልጽ እየታወቀ፣ ከቦታ ጥያቄና ከተራ የታሪክ ሽሚያ ጋር በማላተም ‹‹ቅማንትን እንደቅማንት ማወቅ የጎንደርን ታሪክ መበረዝ ማለት ነው›› በማለት፣ የኢትዮጵያን ገናናና የቆየ ታሪክ የቅማንት ሕዝብ ታሪክ ጭምር እንዳልሆነ በማሰብ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ በአንድ ሕዝብ ብቻ አማካይነት የተሠራ ታሪክ ለማስመሰል ከሚጥሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር የአሉባልታ ዲስኩር ሲነገር ይደመጣል፡፡ ይህ ምን ማለት አንደሆነ ለማንም ስውር አይደለም፡፡
የእዚህን ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ መብት በኃይል ለመደፍጠጥ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሙከራዎች በክልሉ መንግሥት አማካይነት ተፈጽመዋል፡፡ ለአብነት ያህል ‹‹የቅማንት ሕዝብ ሕገወጥ ሠላማዊ ሠልፍ ሊያደርግ ተዘጋጅቷል›› በሚል የፈጠራ ወሬ ይህን ሕዝብ ለማሸማቀቅና ለማስበርገግ አንድ ሻለቃ የመከላከያ ጦር በላይ አርማጭሆ ወረዳ በትክል ድንጋይ ከተማ ከነሙሉ ትጥቁ በሕዝብ መሀል ከሳምንት በላይ እንዲሰፍር ተደርጎ ነበር፡፡ ከሕዝቡ የተሰበሰበ ገንዘብን ያለምንም ሕጋዊ አካሄድ በወረዳው አስተዳዳሪ ትዕዛዝ ወጭ በማድረግ ሠራዊቱ ቀለብ ቀርቧል፡፡ ምናልባት የያኔው የላይ አርማጭሆ ወረዳ አስተዳዳሪ የዘነጉት ነገር ቢኖር ይህ ሕዝብ አሁንም ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ለማስከበር ትግሉን የሚቀጥል መሆኑን ነው፡፡
የተከበሩ አቶ ካሳ
ካለፉት አስከፊ የደርግና የፊውዳል ሥርዓት በባሰ መልኩ የሕዝቦች መብት ይከብረበታል በተባለው በአሁኑ የፌዴራል ሥርዓት የቅማንት ሕዝብ ከፍተኛ በደል እንዳሁኑ ደርሶበት አያውቅም፤ ለወደፊቱም ይደርስበታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በዚህ ሥርዓት የዚህ ሕዝብ በደል የጀመረው ከሽግግር መንግሥቱ መቋቋም ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ይህም ማለት በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት ጥናት አማካይነት እንደ ብሔር ተመዝግቦ በሕዝብ ብዛቱ በ12ኛ ደረጃ ይገኝ ነበረ፡፡ የሽግግር መንግሥቱ አዋጅ 07/1984 ይህን ሕዝብ በግልጽ ከብሔረሰቦች መዝገብ ሰርዞታል፡፡ በ1987 ዓ.ም በተደረገ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ቅማንት ነኝ ብሎ የተቆጠረው ሕዝብ ብዛት 72,259 ሆኖ እያለ ይህን ሕዝብ ወደሌላ ሕዝብ የሚቀይር ወይም ከነበረበት አካባቢ የሚያጠፋ ምንም ዓይነት ተፈጥሯዊ ወይም ሰው ሠራሽ አደጋ ሳይከሰት፣ በ1999 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ቅማንት እንደሌለ ተደርጎ በደባል ማንነት ሥር እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ ይህ በደል እርስዎ በተገኙበት ሕዝብ ላይ ቢፈጸም ምን ይሰማዎት ይሆን?
ክቡር አቶ ካሳ
የቅማንት ሕዝብ በአንዳንድ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት እንደ ብሔረሰብ እንዳይታይና ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፈውን ራስን በራስ ማስተዳደር መብቱ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ተነፍጓል፡፡ በመሆኑም የፌደሬሽን ምክር ቤት በተሰጠው ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን መሠረት የዚህን ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እንዲያስከብርልና እንደሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላችንና ቋንቋችን እንድናሳድግ፣ ትክክለኛ ታሪካችን በራሳችን እንድንጽፍ ብሎም አካባቢያችንን በማልማት ሕዝባችን አሁን ካለበት የኑሮ ደረጃ ወደተሻለ መንገድ ለማሸጋገር እንድንችል፣ የሕገ መንግሥት ምሰሶዎች ብሔር ብሔረሰቦች መሆናቸው ታውቆ፣ የተነፈገውን መብታችንን እንዲያስመልሱልን ስንል ይህን ሕገ መንግሥት ለማምጣት በተሰው ሰማዕታት ስም እንጠይቅዎታለን፡፡

ክብር የኢትዮጵያን ሕዝቦች ከብሔረሰብ ጭቆና ነፃ ለማውጣት ሲታገሉ ለተሰው ሰማዕታት!
No comments:
Post a Comment